[the_ad_group id=”107″]

ጫማ ሰፊዎቹ እና ሀብታሞቹ

እንዲህ መሰለኝ የሚለው ርዕሱ፡፡ የደራሲ ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ድርሰት እንደሆነ አስታውሳለሁ፡፡ ስንተኛው ተረትና ምሳሌ መፅሐፍ ላይ እንደታተመ ግን አላስታውሰውም፡፡ ምን አልባት ስሜ ታደሰን ብጠይቀው ሊነግረኝ ይችል ነበር፡፡ አንድ ሁለቴ ልደውልለት ሞክሬ ኔትወርክ እንቢ ብሎኛል፡፡ ቴሌ ራሱን እንደ ሰይጣን ለሰበብ አሳልፎ ከሰጠ ምን ይደረግ? ኔትወርክ እንቢ አለኝ ጥሩ ሰበብ በህፃንነቴ በታላቅ እህቴ አማካኝነት በቃሌ ያጠናሁት ተረታዊ ድርሰት ነው፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ምንጩ የውጪ ድርሰት ነው ሲሉ ብሰማም እኔ ግን በተመሳሳይ ጊዜ፣ ወይም ቀድመን አሊያም በኋላ ለማሰብ ማን ይከለክለናል? ባይ ነኝና የደራሲ ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ስራ መሆኑን መቀበል ይመቸኛል፡፡ ብቻ ጫማ ሰፊውና ደሀው ሰው (ብዙ ገንዘብ የማይቆጥረው ማለቴ ነው) እና ሐብታሙ ሰው (ብዙ ገንዘብ የሚቆጥረውና የሚያስቆጥረው ማለቴ ነው) በጉርብትና ይኖሩ ነበር፡፡ ድሀውና ጫማ ሰፊው ሰው ጫማውን እየሰፋፋ፣ በስራው እየተደሰተና እየዘማመረ ይኖር ነበር፡፡ እኛም ድሆቹ የተለያዩ የሕይወት ጫማዎችን እየሰፋን በስራችን ተደስተን፣ ሰላም ተሰምቶን እየዘማመርን እንኖር ነበር፡፡ ድሀው ጫማ ሰፊ ሰዎችን ከእንቅፋት፣ ከእሾህ አሜከላ፣ ከአቧራ ከጭቃ እንዲከላከልላቸው – መሄድ እንዲችሉ በጥሩ እንዲራመዱ ጫማቸውን እየጠጋገነ፣ በጫማ ላብ ሽታ፣ በቆሻሻው ሳይመረር እየዘማመረ በደስታ ስራውን ይሰራል፡፡ እኛም ደሀዎቹ ሰዎችን ከመሄድ የከለከላቸውን የተለያየ አይነት የሕይወት ጫማ እየሰፋን በስራችን እነዚያ ለመሄድ የተቸገሩ ሰዎች ችግራቸው ተወግዶላቸው ስናይ ተደስተን እየዘማመርን እንኖር ነበር፡፡ ነበር…

የድሀው ጫማ ሰፊ ጎረቤት የሆነው ሀብታም ሰው የብርና የወርቅ ገንዘቡን ከመቁጠር በስተቀር ስለ ዜማና ዝማሬ ምንም የሚያውቀው የለም፡፡ ውስጡ ያለው ሐብቱ ሁሉ ቢዝቁት የማያልቅ ሀዘንና ተስፋ መቁረጥ ነበር፡፡

ጎረቤት ያለን ሀብታሞቹ ደግሞ አሮጌ ጫማ አንጠግንም፡፡ የሰው ላብ አናሸትም – ቢያስፈልግ አዲሱን ጫማ በፋብሪካ እናመርታለን፡፡ ውሏችን ታች አይደለም፣ መዶሻ ሚስማር አንነካም፡፡ ጨዋታችን ከፋብሪካና ከኮምፒዩተር ጋር ነው፡፡ ብራችንን እንኳን በእጃችን አንቆጥርም፡፡ ቢያስፈልግ በማሽን አለያም በሌላ ሰው እጅ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከሰው ላብ ይልቅ የብር ጠረን ነው አፍንጫችን የሚገባው፡፡ ዝማሬአችን የሳንቲም ቅጭልጭልታ ነው፡፡ ከሰዎች ጋ በሆነ አጋጣሚ ብንገናኝ እንኳን የገንዘብ እዳቸውን ሊከፍሉን ወይም ሸቀጦቻችንን ሊገዙን ነውና ሰዋዊውን ዜማ ማጣጣም ካቆምን ቆይተናል፡፡ በሰው አንደበት የምንሰማው ዜማ እንኳን ቢኖር “ገንዘብ፣ ገንዘብ” ቢዝነስ፣ ቢዝነስ… ፎቅ፣ መሬት፣ ቤት… የሚለውን ነጠላ ዜማ ሊሆን ይችላል፡፡

ከእለታት አንድ ቀን የዚያን ሀብታም ጆሮ አንድ ሰምቶት የማያውቀው ዜማ ጠለፈው፡፡ ልቡም መንፈሱም ከተጠለፈው ጆሮው ጋ አብሮ ሄደ፡፡ አንድ እሱን ከተቆጣጠረው ለየት ያለ ድምፅ፣ በነፍሱ ውስጥ፣ በሁለንተናው እየተንጬረጬረ እንደሚያልፍ የወንዝ ወራጅ ድምፅ፣ ወይም እንደሚንሿሿ የዛፍ ቅጠሎች ወይም… ብቻ የሚያለቅሰውን ነፍሱን ወይም መንፈሱን የሚያባብል ድምፅ ሰማ፡፡ እናማ “ገንዘብ ካለ…” አይደለ ነገሩ? የሚያውቀው መግዛት መሸጥ ነውና ያንንም አባባይ፣ ደስታ ፈጣሪ ድምፅ በብዛት መግዛት አማረው፡፡ ሳይገዛው በሩቁ ከሚሰማው ይልቅ ከፍሎበት በበለጠ ሊያገኘው – የግሉ ሊያደርገው ተመኘ፡፡ ተመኝቶም አልቀረ ወደዚያው ድምፅ ተጓዘና ለዜማው ባለቤት ከፈለው፡፡ በነፃ ያገኘው የነበረውን ይህንን ደስታ ፈጣሪ ድምፅ በገንዘቡ… (እኛ ሐብታሞቹ እኮ ሁልጊዜ ሁሉንም ነገር ገዝተን እንደምናገኘው እናስባለን፡፡ እና ደግሞ እንገዛዋለን…ግን የገዛነው እለት…)

ጠዋት፣ ማታ ከውስጥ በሆነ ዝማሬ እረፍቱን በሚያበስሩ ቃላት የተሞላው ደሀው ጫማ ሰፊ ሀብቴ ብሎ የሳሰበው ይሄ ሀብቱ (ደስታና ሰላምን መዘመር ማንጎራጎሩ) ብዙ ብር መሆኑን ሲያይ ደሀው ጫማ ሰፊ ተገረመ – ደነገጠ! መጀመሪያ ጉሮሮውን ከዝማሬ ያነቀው አንደበቱን የለጎመው ይኸው ድንጋጤ ነበር፡፡ ቀናት መቆጠር ጀመሩ፡፡ በደሀው ጫማ ሰፊ ዝማሬው ጓዙን ጠቅልሎ ወጣ – እንቅልፍና ሰላም ማንም የማይወስድበት የነበሩት ሀብቱ ተሰረቁ፡፡ ጫማ መስፋት ትቶ ዘብ ማደር ሆነ ስራው፡፡ ከሀብታሙ ሰው ያገኘው ገንዘብ እንዳይሰረቅ መጠበቅ፡፡

እኛ የገንዘብ ድሀ ነን ባዮቹ ያለንን ትልቅ ሀብት መረዳት የምንጀምረው ባጣነው ጊዜ ነው፡፡ ለሌሎች በመኖር፣ ቀዳዳቸውን ገመናቸውን በመስፋት የምናገኘው ዜማ ከኛ አልፎ ሌሎችን ይጠግን እንደነበር የምናውቀው ምን አልባት መባነን የቻልን እንደሆን ብቻ ነው፡፡ የያዝነው በነፃ የምንሰጠው፤ ሰላምና ፍቅር እረፍትም ሰጪ ዜማ ነበር፡፡ ግን ዜማቸው የሳንቲም ቅጭልጭልታ የሆኑ ሀብታሞች የኛን ዜማ በገንዘብ ለመግዛት ያሰቡና እሺ ያልናቸው ቀን የኛም የሀብታሞቹም ዜማ እኩል ይጠፋል፡፡ እንቅልፍ አልባ ሆነን መቃተት – መባተት ይሆናል የየዕለቱ የሕይወት ጉዞአችን፡፡ ሰዎች ገና ነካ ሲያረጉን አሮጌውንና ጭንቅላት የሚቧጥጠው ዜማ ማውጣት እንጀምራለን – የኑሮ መወደድ፣ የቤት ኪራይ ዋጋ መናር፣ የምድሪቱ ውጥንቅጥ መብዛት፣ ምን ሰርተን በምን እጥፍ አትርፈን ከነ እከሌ እኩል እንደምንሆን ጥማት፣ ብሶት፣ መብከንከን ይሆናል ዜማችን፡፡ ካልባነንን…

ድሐው ጫማ ሰፊ ግን ባነነ፡፡ እናም በዛገ ቆርቆሮ አልማዙን እንደለወጠ ተሰማው፡፡ ዘብ ያደረለትን ገንዘቡን አውጥቶ ሮጦ ወደ ሀብታሙ ሰው ዘንድ ሄደ፡፡ እየተንገፈገፈም “እንካ ብርህን… እንካ! ሰላሜንና ዝማሬዬን ግን መልስልኝ” በማለት ሰላሙን እና የደስታውን አብሳሪ የሆነውን አንደበቱን የከረቸመበትን መርግ ደንጊያ የሆነውን የከረጢቱን ገንዘብ መለሰለት፡፡ ባነነ፡፡ ባነነ!

ዛሬም እኛ ደሀዎቹ – ግን እጅግ ሀብታሞቹ በተለያዩ አይነት ሀብታሞች ሰላማችንን፣ ደስታችንን፣ እረፍታችንን ተነጥቀን ሊሆን ይችላል፡፡ በምን? እንዴት? ራሳችንን ጠይቀን መልሱን ካገኘነው “እንካችሁ የናንተን የኛን ግን አትንጠቁን” በማለት ዛሬ አሁን ራሳችንን ልናስጥል አይገባንምን?

ጌታን ተቀበሉ!

ዘሪቱ ከበደ በዚህ “ጌታን ተቀበሉ!” በተሰኘው ጽሑፍ ስለ የምስራቹ ቃልና ይህን የምስራች እንዲያደርሱ በእግዚአብሔር ስለ ተጠሩ አማኞች ታብራራለች፤ “እኔም እኅታችሁ በእግዚአብሔር ጸጋና መልካም ፈቃድ፣ የዚህ ሕይወት የሆነው ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አብስሪነት ዕጣ ወደቀብኝ።” ስትል የሕይወት የጥሪ አቅጣጫዋን ታመለክታለች። ተጨማሪ ያንብቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.