[the_ad_group id=”107″]

የራቢ ሃሮልድ ኩሽነር ጥያቄና መልስ

ታትሞ በተሰራጨበት ወቅት፣ በኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ታላቅ አድናቆት ተችሮት የነበረውና፣ “ክፉ ነገር በጥሩ ሰዎች ላይ ሲደርስ”[1] የሚለው መጽሐፍ ከተጻፈ አርባ ዓመታት አልፈውታል። ጸሐፊው ሃሮልድ ኩሽነር የሚባሉ የአሜሪካ ዜጋ ዕብራዊ ሰው ሲሆኑ፣ በሰሜን ምሥራቅ የተባበሩት አሜሪካን አካባቢዎች አክራሪ የዕብራውያን ምኩራብ አስተማሪም ነበሩ። ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ እያለ፣ እንደ ዊኪፒዲያ ሪፖርት ራቢ ኩሽነር ያለፈው ሚያዚያ ወር መጀመሪያ ቀናት በሰማኒያ ስምንት ዓመታቸው ከእዚህች ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የመጽሐፉ አወላለድና የመልእክቱ ሥረ ታሪክ፣ እንዲሁም ራቢ ኩሽነር የላይኛውን ርእስ የመረጡበት ምክንያት፣ አሮን የተባለ ወንድ ልጃቸውን በወጣትነቱ ሞት ስለ ነጠቀባቸው ነበር። ከሴት በኵር ልጃቸው ቀጥሎ የተወለደው አሮን ኩሽነር፣ ከጨቅላነቱ ጀምሮ አንድ ችግር እንዳለበት ወላጆቹ ያውቁ ነበር። ከብዙ ጭንቀት፣ ልፋትና ውጣ ውረድ፣ እንዲሁም የብዙ ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች ደጅ መጥናትና ምርመራ በኋላ፣ የአሮን ተፈጥሯዊ ሕመም በአንድ ሐኪም ታወቀ። ይኸውም፣ ምስኪን ወንድ ልጃቸው በወጣትነቱ የሚያስረጅ በሽታ (“progeria”) ተጠቂ ነበር። በእዚህም ሳቢያ፣ አሮን በፍጥነት ጨቅላ፣ በፍጥነት ሕፃን፣ በፍጥነት ወጣት፣ በፍጥነት ጎልማሳ፣ በፍጥነት አረጋዊ፣ በፍጥነትም ሽማግሌ ሆኖ፣ ሃያ ዓመት ሳይሞላው ሞተ። እንደ ሌሎች ሕፃናት ሳይቦርቅ፣ እንደ ሌሎች ልጆች ትምህርቱን ሳይማር፣ እንደ ሌሎች ወጣቶች ኮሌጅ ሳይገባና ሳይመረቅ፣ አግብቶም ልጅ ሳይወልድ ካለ ዕድሜው ተቀጨ።

ይህን ጥቃት መቀበል ያቃታቸው ራቢ ኩሽነር፣ አሮን ከመሞቱ ሦስት ዓመታት በፊት “ለምን?” በሚል ከባድ ጥያቄ ራሳቸውን በመጠየቅ የመጽሐፉን ዐሳብ ጀመሩት። ብዙ ማለት ቢቻልም፣ ከራቢ ኩሽነር ትላልቅ ጥያቄዎች ውስጥ፣ “ይህ ፈተና ለምን እኔ [እና ቤተ ሰቤ] ላይ ሊመጣ ቻለ?” የሚል ነው። ኩሽነር ብዙ ሺሕዎች አባል የሆኑበት ምኩራብ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ናቸው። ብዙዎችን በእግዚአብሔር ቃል ያጽናናሉ። ከእዚህም ሌላ ራቢ ኩሽነር በጣም ጥሩ ሰው ናቸው። ራቢው መጠጥ አይጠጡ፣ ሀሺሽ መውሰድ ቀርቶ፣ ሲጋራ እንኳን እያጨሱም። አይሰርቁ፣ ሆን ብለውም አይዋሹ። ከሌላ ሰው ጋር ተጣልተው ቢያውቁም፣ አንዲት ነፍስ አጥፍተው አያውቁም። ሌላውን ለመጠየቅ እንጅ፣ በራሳቸው ጥፋት ምክንያት የእስር ቤት ደጁን ረግጠውት አያውቁም።

ስለዚህ “ለምን?” የሚለው ጥያቄ በአእምሯችው ውስጥ ተተከለ። “ከመጀመሪያውኑ ውዱ ልጄ አሮን ለምን እንዲህ ሆኖ ለእኔ ተሰጠኝ?” እና የመሳሰሉትን ዐይነት ጥያቄዎች ራሳቸውን ይጠይቃሉ። በእዚህ ላይ ኩሽነር የሃይማኖት ሰው፣ ራቢ ናቸው፤ ከእርሳቸው ዐልፈው ለሌሎች የሚተርፉ። ለእርሳቸውና ለቤተ ሰባቸው፣ እንዲሁም ለአካባቢያቸውና ለአገር ጭምር መልካምን ይመኛሉ፤ ጥሩ ነገርንም ያደርጋሉ። ለእዚህም የበኵላቸውን ዕለት ተዕለት ጠቃሚና መልካም ነገሮችን በማድረግ ሰላማዊ ኑሮ ይመራሉ። ከሚያውቋቸው ብዙ ሰዎች በኑሮ ሞራልና በአስተሳሰባቸው በጥሩነት ያነሡ አይደሉም። እንዲያውም ከሚያዩትና ከሚሰሙት፣ በዙሪያቸውም ካሉ ብዙ ክፉዎችና ኀጢያተኞች፣ እርሳቸው እጅግ በጣም ሃይማኖተኛ እና በባሕርይም በጣም የተሻሉ ናቸው። ታዲያ፣ ይህ ለእርሳቸው የማይገባ ክፉ ነገር እንዴት እና ለምን ሊደርስባቸው ቻለ?

እንደ እነዚህ እና የመሳሰሉትን ዐይነት ጥያቄዎች፣ ውድ ወንድ ልጃቸው በአፍላ ወጣትነቱ እንደሚሞት ካወቁ ጀምሮ ያስቡ ነበር ማለት ነው። እንደ ማስታውሰውም፣ መጽሐፉን በልባቸው መጻፍ የጀመሩት ከላይ ያሉትን ዐይነት ጥያቄዎችን ከራሳቸው ጋር እየተነጋገሩና እየተጠያየቁ ነበር። ይህም፣ አሮን ከመሞቱ ከሦስት ዓመታት ጀምሮ ነበር። እ.አ.አ. በ1981 ታትሞ የተሰራጨው የራቢ ሃሮልድ የመጀመሪያ ባለ 177 ገጾች መጽሐፍ፣ በሰው ልጅ ምድራዊ ኑሮ ውስጥ እጅግ ከባድና ሞጋች ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክሯል። ብዙ ሚሊዮኖችም የራቢውን መልሶች በጣም አድንቀው ወድደውላቸዋል።

መጽሐፉ መመለስ ከሞከራቸው ጥያቄዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦ “በምድር ላይ ክፉና መከራ ለምን ኖረ?”፣ “እግዚአብሔር መልካም ከሆነ ክፋት ለምን ኖረ?”፣ “ቢኖርም፣ አምላክ ክፋትና መከራን ለምን ፈቀደ?’፣ “ለምንስ ዝም ይላል?”፣ “በተለይ እርሱን የሚያውቁትና የሚያገለግሉት፣ የሚያመልኩት ለምን አስደንጋጭና ድንገታዊ መከራ ይወድቅባቸዋል?”፣ “ጥሩ ሰዎች ከኀጢአተኛና ክፉ ሰዎች እኩል ሊሰቃዩ ይገባቸዋልን?”፣ ወዘተረፈ።

ራቢ ሃሮልድ ኩሽነር ለላይኛዎቹ ዐይነት ጥያቄዎች መልስ መስጠት የጀመሩት፣ የመላ ፍጥረት ፈጣሪ የሆነውን እግዚአብሔር አምላክ ከሉዓላዊ ዙፋኑ በማንሣት ነው። ማለትም፣ የምናመልከው አምላክ እግዚአብሔር፣ “በሁሉ ነገርና በሁላችን ላይ ሉዓላዊ አይደለም” ብለው፣ እግዚአብሔር በፍጥረት ላይ ያለውን ሙሉ ሉዓላዊነት አሳነሱት [ለእኔ ሉዓላዊነቱን “ካዱት”]። ክፋት በምድር ላይ እንዳለ ሳይከዱ፣ መከራ በዘፈቀደ በማንም ላይ ሊደርስ እንደሚችል ገልጸው፣ እግዚአብሔራችን ሁሉን መከራ ማስቆም እንደማይችል በሰላ ብዕራቸው አስረዱ።

የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ፣ የክፋትን ኀይል በሙላት መቆጣጠር እንደማይችል እና ክፋት/መከራ ከእርሱ ፈቃድ ውጭ ሊሆኑ እና ሊከሰቱ እንደሚችል በድፍረት ደመደሙ። ለእዚህ ዐይነት መልሶቻቸው ብዙ እጆች አጨበጨቡላቸው፤ የብዙዎችንም ልብ “አሳረፉ”። ብዙ ሚሊዮኖችም “እሰይ! አሁን መልስ አገኘን!” ብለው ተደሰቱ። ብዙ ብርም የሃሮልድ ኩሽነር ባንክ አካውንት ውስጥ ገባ።

መዝጊያ፦ ራቢ ሃሮልድ ኩሽነር ያነሧቸው ጥያቄዎች እጅግ እጅግ ከባድና አጥጋቢ መልስ የማይገኝላቸው ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቃቸውም ሆነ፣ መልስ ለመስጠት መሞከራቸው አያስወቅሳቸውም፤ መጽሐፍ መጻፋቸውም ያስመሰግናቸዋል። ይህም ሆኖ ግን፣ የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሪና የጌታ አገልጋይ የሆኑት ኩሽነር (የብሉይ ኪዳን ብቻ ቢሆንም)፣ ለጠየቋቸው ከባድ ጥያቄዎች የሰጧቸው መልሶች ትክክል አይደሉም። እንዲያውም በጣም አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ።

አንባቢ፤ የራቢ ኩሽነር መልሶች ለምን ስሕተት እንደ ሆኑ ቢያስቡበት፣ ከሌሎች ጋር ቢወያዩ፤ ፈቃደኛ ከሆኑ ደግሞ፣ ከታች አስተያየት ቢሰጡበት መልካም ይሆናል።


[1] Rabbi Harold Kushner. “When Bad Thing Happens to Good People” (1st published 1981)

Amare Tabor


አማረ ፈቃደ ታቦር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በስታትስቲክስ፣ ሁለተኛውን በኮምፒውተር ሳይንስ የሠሩ ሲሆን፣ መጻሕፍትን የማንበብ ልምድና የመተርጎም ዝንባሌ አላቸው። በተለይ በክርስትና ዙሪያ የተለያዩ መጣጥፎችን በመጻፍና በመተርጎም ይበልጥ ማገልገልን ይሻሉ። 
E-mail: taboramare@gmail.com

Share this article:

ስለ ዘፈን

ዘሪቱ ከበደ በሕንጸት ድረ ገጽ ላይ ለንባብ ባቀረበችው በዚህ ጽሑፍ፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ እስከ አሁን በዘለቀው የዘፈን ጕዳይ ላይ ብያኔዋን ትሰጣለች። “ይህን ጕዳይ ሳነሣ ለዘፈን ጥብቅና ልቈም ፈልጌ አይደለም። ይሁን እንጂ፣ እውነትን መናገርም ሆነ መነጋገር አስፈላጊ እንደ ሆነ ደግሞ አምናለሁ።” የምትለው ዘሪቱ፣ ወደ ጌታ የመጣችበትን ሂደትና የተለማመደችውን መንፈሳዊ ሕይወት እያስቃኘች፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ በርእሰ ጕዳዩ ላይ ሊኖረው ስለሚገባ ግንዛቤ ዐሳቧን ታካፍላለች፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው ያለቻቸው ማስረጃዎቿንም ታቀርባለች። በዚህ ብቻ አታበቃም፤ በሙዚቃ ጥበብ ውስጥ መዝለቅ የሚሹ ክርስቲያን ወገኖች ሊኖራቸው ስለሚገባ መንፈሳዊ አመለካከትና መውሰድ ስለሚጠበቅባቸው ጥንቃቄ የምክር ቃል ታካፍላለች።

ተጨማሪ ያንብቡ

“የዘመናችን” ቤተ ክርስቲያንና የተሐድሶ ጥያቄ፦ ተግዳሮቶችና ዕድሎች!

“የወንጌል ተልእኮ ብዙውን ጊዜ ለውጪው ዓለም ብቻ እንደ ሆነ ስለምናስብ፣ ወንጌልን ይዞ ወደ ውጭ መሮጥን ቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ ሰጥታ ስትተጋበት ትታያለች። ነገር ግን፣ ‘ታላቁ ተልእኮ’ የሚመነጨው ከ’ታላቁ ትዕዛዝ’ መሆኑን እንዘነጋለን። ‘… ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ’ ያለው ጌታ አስቀድሞ፣ ‘“ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤” ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዞች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።’ (ማቴ. 22፥37-40) ሲል አስረግጦ ነግሮናል።”

ተጨማሪ ያንብቡ

ማንነት እና ስንክሳሩ

“አብሮነት ራሱን የቻለ ድብለቅ ነው፤ ራስ በራስ ሳይሆን እርስ በርስ። ስለዚህ የስሜት ብስለት ይጠይቃል፤ ግለ ሰቦች በስሜት በሳል ሲሆኑ የራስም ሆነ ከሌላው ጋር የሚኖራቸው ትምምን ከፍ ይላል” ሰሎሞን ጥላሁን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ካሰፈረው

ተጨማሪ ያንብቡ

2 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

 • ትክክለኛ ጥያቄ ነው። ሃሳባቸውም ትክክል ነው። ትክክል የሆነው ግን በእርሳቸው አስተሳሰብ ነው።

  እኔ ግን አቅም የለኝምና እግዚአብሔር የፈለገውን የማድረግ ፈቃድም ብቃትም አለው ብዬ ሃሳቤን እናገራለሁ። ሰይጣን በራሱ ስልጣንም ፈቃድም መብትም የለውም። እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም። እርሱ ሳያውቅ ምንም ነገር አይሆንም አይፈጠርምም። ምን አልባት ሰይጣን ጉዳይ አስፈጻሚ ይመስለኛል።

  ተጨማሪ ጥያቄ ልጠይቅ:
  አንድ ሰው መሞቱ ካልቀረ ለወራት ለአመታት ታሞና ማቆ ለምን ይሞታል? ወዲያውኑ ወይም በሳምንቱ ለምን አይሞትም?

  ስንት ኢኮኖሚ አቃውሶ ፣ ተስፋ አስቆርጦ ብዙ ነገር ከተፈጠረ በኋላና ተስፋ ከተቆረጠበት ፣ በተለይም መቼ ነው የሚሞተው ወደ መባል ደርሶ ለምን ይሞታል?

  ሰው መትረፉ ካልቀረ ለምን ይሰቃያል ዋጋስ ያስከፍላል?

  ብዙ ጥያቄ አለ ግን ፣ የመጠየቅ እንጅ የመመለስ ስልጣንና እውቀት የለንም።

  ሌላም ጥያቄ አለ ፣ ግን አይጠቅምም ጭንቅላት ያዞራል።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.